ከልጅነቱ የአርሰናል ወዳጅ ሆኖ ያደገው ዊሊያም ሳሊባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዚህ ወቅት ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የመሐል ተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው ፈረንሳዊው ዊሊያም ሳሊባ፡፡
መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የተወለደው ሳሊባ እንደ ማንኛውም ታዳጊ በፓሪስ በምትገኝ ቦንዲ መንደር ውስጥ መንገድ ላይ ኳስ እየተጫወተ ነው ያደገው፡፡
በሳሊባ የእግር ኳስ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣው የኪሊያን ምባፔ አባት ዊልፍሬድ ምባፔ ነው፡፡
የኪሊያን ምባፔ አባት ዊልፍሬድ ምባፔ ዊሊያም ሳሊባን በ6 ዓመቱ መንገድ ላይ ሲጫወት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተው።
በቦንዲ መንደር ኪሊያን ምባፔ ሳይቀር የመጀመሪያ የእግር ኳስ ሕይወት ስልጠና የጀመረበትን የቦንዲ አካዳሚን ሳሊባ በዊልፍሬድ አማካኝነት መቀላቀል ችሏል፡፡
ከኪሊያን ምባፔ ጋር በአንድ ትምህርት ቤት በመማር እድገቱን ያደረገው ሳሊባ 13 ዓመት ሲሞላው ቦንዲ አካዳሚን በመልቀቅ ሞንትፈርሚልን ተቀላቅሏል፡፡
ከሁለት ዓመታት የሞንትፈርሚል ቆይታ በኋላ የሴንት ኢቴንን ከ17 ዓመት በታች ቡድን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
በሴንት ኢቴን ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ በመቻሉ በ17 ዓመቱ የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል ኮንትራት ከሴንት ኢቴን ጋር ተፈራርሟል።
በመጀመሪያ ዓመት የሴንት ኢቴን ቆይታው የመድፈኞቹን እና የቶተንሃምን ትኩረት የሳበው ሳሊባ በ27 ሚሊየን ፓውንድ አርሰናልን ተቀላቅሏል፡፡
ሳሊባ ፊርማውን ለአርሰናል ቢያኖርም ለአንድ የውድድር ዓመት በውሰት ውል በዚያው በሴንት ኢቴን ቆይቷል፡፡
የውሰት ውሉን ጨርሶ ወደ አርሰናል የመጣው ሳሊባ ዋናውን ቡድን ቢቀላቀልም ብዙም ሳይቆይ የአርሰናል ከ23 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
ከዚያ በመቀጠል ለኒስ እና ማርሴ በውሰት ከተጫወተ በኋላ በ2022/23 የውድድር ዘመን የአርሰናል ዋናውን ቡድን መቀላቀል ችሏል፡፡
ለአርሰናል ፊርማውን ባኖረ በትንሽ ጊዜያቶች ልዩነት አባት እና እናቱን በሞት ያጣው ሳሊባ ጥሩ ሕይወት ለማሳለፍ ዓመታትን ጠብቋል፡፡
ገና ሕልሙን መኖር ከመጀመሩ የሚወዳቸውን እናት እና አባቱን በሞት ቢያጣም ሥራውን በታታሪነት ይከውን ነበር፡፡
ሳሊባ የውሰት ውሉን አጠናቅቆ ወደ አርሰናል በመመለስ ለዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን በ2022 በፕሪሚየር ሊጉ ማድረግ ችሏል፡፡
በሚኬል አርቴታ ስር ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ሳሊባ የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት አርሰናል የዋንጫ ተፎካካሪ እንዲሆን ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በምባፔ አባት ምክር እና የእግር ኳስ እርዳታ ያደገው ሳሊባ አሁን በትራንስፈር ማርኬት መሰረት በዚህ ወቅት 90 ሚሊየን ዩሮ ዋጋ የሚያወጣ ተጫዋች ሆኗል፡፡
በዚህም ዊሊያም ሳሊባ ዓለም ላይ ካሉ ውድ የመሐል ተከላካዮች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
የፈረንሳይ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ እያገለገለ የሚገኘው ሳሊባ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ እስከ ፍጻሜ ድረስ መጓዙ ይታወሳል፡፡
ፈረንሳዊው የመድፈኞቹ ኮከብ ዊሊያም ሳሊባ በፈረንጆቹ 2001 በዛሬዋ ዕለት ነው የተወለደው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ