በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ወደ ትግበራ የሚገቡበት ፍጥነት ጨምሯል – ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እየሰራች ባለችው ሪፎርም የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ወደ ትግበራ የሚገቡበት ፍጥነት ጨምሯል አሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)።
ኮሚሽነሩ ይህንን ያሉት በ4ኛው “በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ሪፎርም እየተመራች አሰራሮችን፣ ህጎች እና የትግበራ ፍጥነትን እያሻሻለች መሆኗን ገልጸው÷ በዚህም ኢንቨስተሮች ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበት ከባቢ እያደገ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ሦስተኛው “በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” ፎረም ከ58 በላይ ሀገራት መወከላቸውን ጠቅሰው÷ በወቅቱ ከአምስት ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመቱ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ተፈርመዋል ነው ያሉት፡፡
ስምምነት የተፈረመባቸው ኩባንያዎችም በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገና ምቹ አሰራሮች እየተዘረጉበት ያለ በመሆኑ ኢንቨስተሮች በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ ኢ ሰርቪስ በተለያየ ደረጃ እየተሰጠ ከአስተዳደር ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በቅርቡ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚጀመርና ፎረሙም ልምድ ልውውጦች የሚደረጉበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
በለይኩን ዓለም