Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ስልታዊ አጋርነት የሚያሳድግ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ ተፈራርመውታል፡፡

ስምምነቱ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላትን ኦፕሬሽናል ዝግጁነት ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ብቃት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።

በዚህም የዓለም አቀፍ የሰላም ድጋፍ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ት/ቤት የሚሰጡ የሥልጠናዎች እና የምርምር ተግባራት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ማዕከል የሚሰጡ የስልጠና ሰርተፊኬቶች በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት ዘንድ የላቀ ዕውቅና እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

ለእቅዱ ስኬትም የፈረንሳይ መንግስት አስፈላጊውን የቴክኒክና የማቴሪያል ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የተጠቆመው፡፡

በተለይም ሰላም አስከባሪዎች በጦር ሜዳ የሚያጋጥሟቸውን የፈንጂ አደጋዎች የመከላከል አቅማቸውን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ደህንነት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ ይበልጥ ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘላቂ ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.