Fana: At a Speed of Life!

ኢራን የአሜሪካ እግረኛ ወታደሮችን ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ ነኝ አለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን የሀገሪቱን ምድር በሚረግጡ የአሜሪካ እግረኛ ወታደሮች ላይ እሳት ለማዝነብ በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

አንደኛ ወሩን ያስቆጠረው እስራኤልና አሜሪካ ከኢራን ጋር እያደረጉት የሚገኘው ጦርነት አሁንም በርካታ ጉዳቶችን እያስከተለ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የቀጣናው ጦርነት እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት አሜሪካ ከ3 ሺህ 500 በላይ እግረኛ ወታደሮችንና የጦር መርከቧን በመካከለኛው ምሥራቅ አሰማርታለች፡፡

የዋሺንግተን እግረኛ ወታደሮች በኢራን ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸውንም የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡

ይህን ተከትሎም ኢራን በቀጣናው ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ በሚል ወደ መካከለኛው ምስራቅ የደረሱ የአሜሪካ ወታደሮችን በተጠንቀቅ እየጠበኩ ነው ብላለች፡፡

የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሃማድ ባግሄር ጋሊባፍ ÷ አሜሪካ ለንግግር ፍላጎት እንዳላት እየገለጸች በቴህራን የእግረኛ ወታደራዊ ዘመቻ ለመካሄድ መዘጋጀቷን ኮንነዋል፡፡

የኢራን ጦር የትኛውንም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነው ያሉት አፈ ጉባዔው ÷ ጦሩ ወደ ኢራን በሚገቡ የአሜሪካ እግረኛ ወታደሮች ላይ እሳት ለማዝነብ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና በባህሬን የአልሙኒየም መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ቴህራን በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት የራዳር መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሷ ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ እስራኤል በቴህራን ወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያዎችን እና የጦር መሳሪያ ማምረቻ ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሟን ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል ቱርክዬ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነት ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በፓኪስታን እንደሚመክሩ ተሰምቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.