Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ባለሃብቶች በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዘርፉ ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ከኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ማሕበረሰብና ትብብር ኮሚቴ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እና ቻይና የረጅም ዘመን ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በሎጂስቲክስ፣ በሕዝብ ትራንስፖርትና በአዲስ የሃይል አማራጭ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የቻይና ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ አውቶሞቢሎችን ወደ ሀገር እንዳይገቡ በማድረግ ትልቅ ርምጃ መውሰዷን አብራርተዋል፡፡

ርምጃው ወደ ታዳሽና አዲስ የሃይል አማራጭ ለመሸጋገር ያለመ እንደሆነ ማስረዳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይ በባቡር፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሃይል መሙያ መሰረተ ልማት፣ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በተፈጥሮ ጋዝ መቀየር ላይ ሰፊ የኢንቨስትመንት እድል መኖሩን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ማሕበረሰብና ትብብር ኮሚቴ አመራሮች በበኩላቸው÷ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመገንባት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የመቀየር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሃይድሮጅን በሚሰሩ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.