Fana: At a Speed of Life!

ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ለዘላቂ እድገት…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘላቂ እና የማይበገር ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓትን ገቢራዊ ማድረግ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም ሰፊ የግብርና፣ የሰው ኃይል እንዲሁም ጠንካራ የታዳሽ ኃይል መሰረት ያላት መሆኑ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

የለውጡ መንግስት ይህንን በመገንዘብ በአምስቱ የኢኮኖሚ ዓምዶች ማለትም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተግባራዊ ባደረገው የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓት አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡

ቀደም ሲል በግብርና ላይ መሰረት ያደረገውን የኢኮኖሚ ስርዓት በማስፋት በቱሪዝም፣ በኢነርጂ፣ በአገልግሎትና አምራች ዘርፎች በተከናወኑ ሰፋፊ ስራዎች አበረታች እመርታ ተመዝግቧል፡፡

ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በመላ ሀገሪቱ የተከናወኑ ዐይን ገላጭ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋት ስራዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድን የመሳሰሉ መርሐ ግብሮችን በማስተዋወቅ ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማዘመንና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመገንባት የቱሪዝም ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ ማሳደግ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ከ700 ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በማስተናገድ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት የሚችሉ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

ከ47 በመቶ ያልተሻገረውን የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ወደ 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡

በንቅናቄው አማካኝነት በዚህ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ያወጡ የነበሩ ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ተመርተዋል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ በማዕድን ዘርፍ የ30 በመቶ የገቢ ጭማሪ የተመዘገበ ሲሆን፥ የብረት ምርት 36 በመቶ እንዲሁም ሲምንቶ ምርት 28 በመቶ ጨምሯል፡፡

የልማት ስራዎች በቴክኖሎጂ ካልታገዙ በቀር በሚፈለገው ፍጥነት እድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል የተረዳው የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡

በዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን ተደራሽነት በማስፋት እንዲሁም የኅብረተሰቡን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በማሳደግ ተጨባጭ ሂደቶችን ተራምዷል፡፡

በለውጡ ጅማሬ 37 ሚሊየን የነበረው የሞባይል ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር አሁን ላይ ከ97 ሚሊየን የተሻገረ ሲሆን፥ የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥርም 58 ሚሊየን ደርሷል።

የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥን ማዕከል ባደረገው የግብርና ዘርፍም የበጋ መስኖ የስንዴ ልማትን ጨምሮ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በግማሽ በጀት ዓመቱ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘቱም የዘርፉን ውጤታማነት የሚያመላክት ነው፡፡

በአጠቃላይ የለውጡ መንግስት በአንድ ዘርፍ ላይ ሳይወሰን ለኢትዮጵያ ዘላቂና የማይበገር ኢኮኖሚ መሰረት የሚጥሉ የብዝሃ ዘርፍ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.