የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ከሦስት ክለቦች ጋር ያሳካ ብቸኛ ተጫዋች – ክላረንስ ሲዶርፍ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ክላረንስ ሲዶርፍ የዓለም እግር ኳስ ከተመለከታቸው ምርጥ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡
ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን በጀመረበት የሀገሩ ክለብ አያክስ አምስተርዳም የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎችን በማሸነፍ ስኬታማ ጊዜ አሳልፏል፡፡
ሲዶርፍ ከአያክስ በተጨማሪ ከሪያል ማድሪድ እና ኤሲሚላን ጋር የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን በማሳካት በትልቁ አኅጉራዊ መድረክ ከሶስት ክለቦች ጋር ሻምፒዮን መሆን የቻለ ብቸኛው ተጫዋች ነው፡፡
በአያክስ ስኬታማ ሦስት የውድድር ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ቀጣይ መዳረሻው የጣሊያኑ ክለብ ሳምፕዶሪያ ነበር፡፡
በሳምፕዶሪያ ለአንድ የውድድር ዓመት ከተጫወተ በኋላ የስፔኑን ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ መቀላቀል ችሏል፡፡
በማድሪድ በቆየባቸው ዓመታት በ159 ጨዋታዎች 20 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ እና የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
በድጋሚ ወደ ጣሊያን በመመለስ ሦስት የውድድር ዓመታትን በኢንተር ሚላን ካሳለፈ በኋላ ሌላኛውን የሚላን ክለብ ኤሲሚላን ተቀላቅሏል፡፡
የቀድሞ የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ሲዶርፍ አብዛኛውን የእግር ኳስ ሕይወቱን ያሳለፈውና በርካታ ስኬቶችን የተቀዳጀው በጣሊያኑ ክለብ ኤሲሚላን ነበር፡፡
ሲዶርፍ ከኤሲሚላን የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ሲሆን፥ በክለቡ በቆየባቸው 10 የውድድር ዓመታት 432 ጨዋታዎችን አድርጎ 62 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከክለቡ ጋር የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ፣ የጣሊያን ሴሪ አ፣ ኮፓ ኢታሊያ፣ የጣሊያን ሱፐር ካፕ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ከክለብ ስኬቱ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በፊፋ እና በአውሮፓ የዓመቱ ምርጥ ስብስብ ውስጥ መካተት የቻለው ኔዘርላንዳዊው ኮከብ በፈረንጆቹ 2006/7 የውድድር ዓመት የአውሮፓ የዓመቱ ምርጥ አማካይ ሽልማትን አሸንፏል፡፡
ከፈረንጆቹ 1994 ጀምሮ እስከ 2008 ድረስ በሀገሩ ማልያ 87 ጨዋታዎችን አድርጎ 11 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ተጫዋቹ በእግር ኳስ ሕይወቱ መጨረሻ ለብራዚሉ ክለብ ቦታፎጎ ከተጫወተ በኋላ በፈረንጆቹ 2014 ጫማውን መስቀሉ ይታወሳል፡፡
ክላረንስ ሲዶርፍ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት በመግባት ኤሲሚላን እና ዲፖርቲቮ ላኮራኛ የመሳሰሉ ክለቦችን እንዲሁም የካሜሩን ብሔራዊ ቡድንን ማሰልጠን ችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በኢራኑ ክለብ እስቴግላል ቴህራን ከፍተኛ የስፖርት አማካሪ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከምንጊዜም ምርጥ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ክላረንስ ሲዶርፍ በፈረንጆቹ 1976 በዛሬዋ ዕለት ነበር የተወለደው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ