በለውጡ የተለወጠችው ሀረር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መጋቢት 24 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበትና የለውጥ ብርሃን የታየበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ይህ የለውጥ ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ ተጨባጭ ስኬቶችን በማስመዝገብ ቀጥሏል።
በተለይም ሀገራዊ ስብራቶችን የመጠገንና የልማት ጥማትን የማርካት ጉዞ በታሪካዊቷ የሀረር ከተማ ደምቆ ታይቷል።
ሀረር የዚህ ለውጥ ቀዳሚ ተጠቃሚና የፍሬው ማሳያ በመሆን በታሪኳ አይታው በማታውቅ ፍጥነትና ጥራት ታላቅነቷን የሚያረጋግጡ የለውጥ ስራዎችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
ሀረር ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም ታሪኳን በሚመጥን ደረጃ ሳታድግ ቆይታለች፤ ከለውጡ ወዲህ ግን ይህ ታሪክ በእጅጉ ተቀይሯል።
በእነዚህ የለውጥ ዓመታት አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን ዓለም አቀፉ የጀጎል ቅርስ ከአደጋ መታደግ ተችሏል።
አባዲር ፕላዛና ኑር ፕላዛን ጨምሮ በመልሶ ማልማት የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች የተመቸች እንድትሆን አስችሏታል፡፡
በከተማዋ በኮሪደር ልማት ከተሰሩ መካከል ሰፋፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶች የአረንጓዴ እና የመዝናኛ ስፍራዎች ይጠቀሳሉ።
በተሰሩ ሁሉን አቀፍ ስራዎችም ሀረር ዛሬ ላይ ለመጎብኘት የምታጓጓ ከተማ ሆናለች።