Fana: At a Speed of Life!

የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አሉ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የ2018/19 በጀት ዓመት ሀገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ የክልሎች ግብርና ቢሮ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
አቶ አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ሒደትን ለማሳለጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት በፍጥነት የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ ነው።
ለዘንድሮው የበልግና የመኸር እርሻ በቂ የማዳበሪያ አቅርቦት ቢኖርም ለቀጣይ ዓመት የግብርና ግብዓቶች ዋጋ መናር ምላሽ ለመሥጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ከአፈር ማዳበሪያ ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርት ጅማሮን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በየክልሎቹ ያሉ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የማዳበሪያ ሥርጭቱ አርሶ አደሩ ጋር በወቅቱ እንዲደርስ ለየት ያለ የንቅናቄ እቅድ በመንደፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ጅቡቲ የደረሰውን ጨምሮ 20 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አብራርተዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ቀውስ ምክንያት የ2018/19 በጀት ዓመት የሰብል እና የሆርቲካልቸር ልማት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ እንደሚጀመር ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
ሁሉምን ክልሎች ባላቸው የተፈጥሮ ጸጋ ልክ በማልማት የተጀመረውን ሒደት በተጨባጭ ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተደረገው ሰፊ ጥረት በዘንድሮው ዓመት ሙሉ በሙሉ በሴፍቲኔት መርሐ ግብር ሥር ይደገፉ የነበሩ ዜጎች ከተረጂነት መውጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ፎገራ ወረዳ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የሩዝ ልማት አመቺ ሥነ ምሕዳር ወዳለባቸው ሌሎች ክልሎች በማስፋት ምርታማነቱን ማጠናከር መቻሉን አንስተዋል።
አሁን ላይ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ጫና ተቋቁሞ ምርትና ምርታማነትን ለማስቀጠል የሚመለከታቸው አካላት በትኩረትና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.