ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትነቷን በብቃት ተወጥታለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትነቷን በብቃት ተወጥታለች አለ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፥ ኢትዮጵያ 47 አባል ሀገራት ያሉት የዚህ ምክር ቤት አባል በመሆን ለሦስተኛ ጊዜ ተመርጣ በንቃት እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።
እንዲሁም የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የመጀመሪያውን የአመራር ኃላፊነት በብቃት ተወጥታለች ነው ያሉት።
ምክር ቤቱ በጄኔቫ ሲያካሂድ በቆየው 61ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አንስተው፤ በአባል ሀገራት ከቀረቡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች 38ቱ ውሳኔዎች የተላለፈባቸውና ከእነዚህ ውስጥም ሰባቱ ሀገር ተኮር እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ከሀገር ተኮር ውሳኔዎች መካከል ከዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት፣ ቤላሩስ፣ የሶሪያና ጎላን አካባቢ ባሉ ጉዳዮች፣ በፍልስጤም እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የተገናኙ ጉዳዮች እንደሚገኙና አባል ሀገራቱ ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም በመነሳት የመደገፍና የመቃወም ውሳኔ ማሳለፋቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያም እንደ አባል ሀገር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አቋሟን ማንጸባረቋንና በመርህ ደረጃ ሀገር ተኮር ውሳኔን እንደማትደግፍ አስረድተው፤ እንደዚህ ያሉ ውሳኔዎች ከዚህ ቀደም እንደነበሩና ኢትዮጵያ እንደምትቃወመው አመልክተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረች ጊዜና ባልተስማማችበት ጉዳይ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገራት በጋራ እንዲቀለበስ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
እንደዚህ ያሉ ሀገር ተኮር ጉዳዮች የሚመለከታቸው ሀገራት ሳይስማሙባቸው የሚቋቋሙ፣ የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ሥልጣንና ሚና የሚያጣቅሱ እንዲሁም የምርመራና የዓለም አቀፍ ዳኝነት ይዘት ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሀገርን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ሀገር ተኮር ውሳኔዎችን በመርህ ደረጃ እንደማትደግፍ በማንሳት፥ በጉባኤው ያሳለፈችው ውሳኔም ይህንኑ የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ፍልስጤም እና እስራኤልን በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት መድረክ ስታራምድ የቆየችውን አቋም አሁንም ማስቀጠሏንና የሁለት ሀገርነት መርህን በመደገፍ ከሁለቱም ጋር መልካም ግንኙነት ያላት መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የፍልስጤምን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንደምትደግፍ ጠቅሰው፥ ይህንንም በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ የተላለፈውን የፍልስጤም የራስ ገዝነት ውሳኔ (HRC/61/L.37) ደግፋ ድምፅ መስጠቷን ተናግረዋል።
የሁለት ሀገርነት መፍትሔውም በዘላቂነት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤዎችና በጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች መሰረት እንዲተገበር አሳስባለች ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በሌላ በኩል በጉባኤው በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ከአየር ትራንስፖርት፣ ከመርከቦች እንቅስቃሴ፣ በቀጥታ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረውን ጫናና ስጋት ለጉባኤው መግለጿን አጽንኦት ሰጥተዋል።
አፋጣኝ ተኩስ አቁም እንዲደረግና መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ ማቅረቧንም ገልጸዋል።