ኢትዮ ቴሌኮም ߵቶሎߴ የተሰኘ የፈጣን መንገድ የክፍያ ሥርዓት በቴሌብር አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ߵቶሎߴ የተሰኘ የፈጣን መንገድ የክፍያ ሥርዓት በቴሌብር አስጀምሯል፡፡
ኩባንያው ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ዘመናዊ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተግባራዊ አድርጓል።
ዲጂታል የክፍያ ሥርዓቱ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ባለው የአዲስ አበባ – አዳማ ፈጣን መንገድ ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ በማቀናጀት የተጠቃሚዎችን ተሞክሮ ለማላቅ የሚያስችል ነው፡፡
የኢንተርፕራይዙ ስራ አስኪያጅ ሙስጠፋ አባሲመል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አዲሱ የአገልግሎትና የቅጣት ክፍያ አስተዳደር ሥርዓት ቀደም ሲል በእጅ ይከናወን የነበረውን አሠራር ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ የአውቶሜሽን አሰራር የሚተካ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በዲጂታል መሰረተ ልማት ውስንነት ምክንያት መሰል የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸው፥ አሁን ላይ ኢንተርፕራይዙ ሙሉ ለሙሉ ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነ የክፍያ ስርዓት ወደ ስራ አስገብቷል ነው ያሉት።
ኢትዮ ቴሌኮም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሰረት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን ግልጽና የአሰራር ቅልጥፍና የሰፈነበት የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በዚህም በቴሌብር ሱፐርአፕ አማካኝነት ክፍያዎችን በራስ አገዝ ቴክኖሎጂ ተቀናሽ በማድረግ ተሽከርካሪዎች ለክፍያ ሳይቆሙ በቀጥታ እንዲያልፉ በማድረግ ጉዞውን ፈጣን እና ምቹ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በመራኦል ከድር