ለሀምበሪቾ መንደር ፕሮጀክት ግንባታ የሀብት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሀምበሪቾ መንደር ፕሮጀክት ግንባታ የሀብት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተከናወነ ይገኛል፡፡
መርሐ ግብሩ “የጋራ ቤታችንን በጋራ እንገነባለን” በሚል መሪ ሃሳብ ለፕሮጀክቱ የሚውል 1 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ያለመ ነው፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ እንደስያሜው ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ የሚወክል ዲዛይን የያዘ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ የእንግዳ ማረፊያ፣ ሙዚየም፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ የተለያዩ ዘመናዊ የግብርና ልማት ስራዎችና ሌሎች ግንባታዎችን ያቀፈ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ፕሮጀክቱ ከቱሪስት መስህብነት ባሻገር የአካባቢውን የአኗኗር ሁኔታ የሚያሻሽል ነው ብለዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው በአካባቢው ያለውን ሀብት በመጠቀም ተራራውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እንዲሰራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
የሀምበሪቾ ሰባት ተራሮች በህብረት የፈጠሩት ሰንሰለታማ መልከዓ ምድር ላይ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተጎበኘ በኋላ ልዩ ትኩረት ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግበሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎቸ፣ የአካባቢው ተወላጆች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
በእየሩሳሌም አበበ