Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና እና የአውሮፓ ህብረት የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት እና የአውሮፓ ህብረት የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ-አውሮፓ ህብረት የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት እና የአውሮፓ ህብረት የተፈራረሙት የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ስምምነት የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማሳለጥ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
እንዲሁም በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል።
ስምምነቱ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 አካል የሆነውን የአህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና ለማጠናከር የተደረገ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተገልጿል።
ይህ ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል እንደ ከፍተኛ ደረጃ የምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እና ንግድ ውይይት ያሉ መድረኮችን ጨምሮ የባለብዙ ወገን ተሳትፎን ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
በተጨማሪም ስምምነቱ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ በላይ ዋጋ ያላቸው ከ80 በላይ ፕሮጀክቶችን ያካተተ ሲሆን፤ የአውሮፓ ባለሀብቶች በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እና በተለያዩ ዘርፎች እሴት ለመጨመር እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
በመሳፍንት ብርሌ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.