ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስቀጠል ትብብሯን ታጠናክራለች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ኢኮኖሚያዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከፈረንሳይ ግምጃ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ግንኙነት ያለውን ስትራቴጂካዊ ፋይዳ በማስመልከት መክረዋል፡፡
በተጨማሪም ውይይቱ ሀገራቱ የልማት ትብብራቸውን ማሳደግ፣ የማክሮኢኮኖሚ ትብብር ስለሚያድግበት ሁኔታ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ የእዳ ሽግሽግ ድጋፍ ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመደገፍ በዓለም ባንክ እና በአይኤምኤፍ በኩል ተቀራርቦ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
በተጨማሪም ፈረንሳይ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የሁለትዮሽ ስምምነት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ እና ከግል አበዳሪዎች ጋር የሚደረገውን ቀጣይነት ያለው ድርድርን ጨምሮ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የብድር አያያዝ በማሳደግ ረገድ ለምትጫወተው ቁልፍ ሚና አጽንኦት ተሰጥቷል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ ለመደገፍ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማስቀጠል ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።