Fana: At a Speed of Life!

የሕብረት ሥራ ማህበራት በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና የሚያጎለብት ተግባር ተከናውኗል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሕብረት ሥራ ማህበራት በሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና የሚያጎለብት ተግባር ተከናውኗል አሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)።

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ 2ኛውን ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ በተለያዩ ከተሞች ማካሄድ ጀምሯል።

በሀዋሳ ከተማ የህብረት ሥራ ማህበራት የሪፎርም ንቅናቄ መድረክ የፌዴራል እና የክልል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ከተሰሩ ሥራዎች መካከል የህብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀትን ማጠናከርና ውጤታማ ማድረግ አንዱ ነው።

የህብረት ሥራ ማህበራት ለዜጎች ቀጥታ ተጠቃሚነትና ውጤታማነት እስከ ቀበሌ ወርደው መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የእውቀት፣ የሀሳብ፣ የልምድ እና ገንዘብ መደመር ለወሳኝ የህብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀት ውጤታማነት አጋዥ ሆኖ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረት ሥራ ማህበራት የአስተሳሰብ፣ የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የአመራር ሪፎርም ካደረጉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ መሆኑን አንስተዋል።

ማህበራቱ የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል ወሳኝ በመሆናቸው ሚናቸውን ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

26 ሚሊየን ዜጎች በ89 ሺህ ማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ እንደሚገኙም ተገልጿል።

የፌደራል ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሺሰማ ገ/ ስላሴ በበኩላቸው፥ የሕግ ማዕቀፍ እና ፍኖተ ካርታ ማሻሻል ዘርፉን ለማጠናከርና ለማደራጀት የተከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በመቅደስ አስፋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.