Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ እና ሲገቡ የተያዙ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ህጋዊ ርምጃ ተወስዷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ እና ሲገቡ የተያዙ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ህጋዊ ርምጃ ተወስዷል አለ።
አገልግሎቱ በፓስፖርት፣ በቪዛ፣ በትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ፣ በአየርና በየብስ ድንበር ቁጥጥርና ሌሎች አገልግሎቶች ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በወቅቱ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአመራርና ሰራተኞችን አቅም ለማጎልበት የሚያግዝ ስልጠና ለ1 ሺህ 700 አባላት ተሰጥቷል።
ስልጠናው ሳይበር ደህንነት፣ ዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የተገልጋዮች አያያዝ እና የግጭት አፈታት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባን በተመለከተ በ9 ወራት 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩነቶች በመመዝገብ የዕቅዱ 88 በመቶ መሳካቱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩነቶችን በወቅታዊ ምዝገባ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
የምዝገባ ስርዓቶችን ለማዘመን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የምዝገባ ስርዓት በማበልፀግ በአዲስ አበባ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ በክልል ከተሞች ለማስፋፋት እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይህም የአገልግሎት ተደራሽነትና ፍጥነትን ያሳድጋል፣ ለአስተዳደርና ለፍትህ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች ይገኙበታል እንዲሁም የውሳኔ አሰጣጥ ተዓማኒነትን ያረጋግጣል ብለዋል።
በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ በክትትልና ቁጥጥር ስራ 4 ሺህ 576 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 10 ሺህ 530 ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ሊገቡ እና ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ተይዘው ህጋዊ ርምጃ ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት።
የውጭ ዜጎች ምዝገባ ቁጥጥርን በተመለከተ 42 ሺህ 809 በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ዜጎችን ህጋዊነት ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸው፤ 3 ሺህ 638 የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ከህግ ውጭ ፓስፖርት ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ቁጥጥር እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።
5 ሚሊየን 433 ሺህ 871 ገቢና ወጪ መንገደኞችን በየብስና በባህር ማስተናገድ መቻሉን እና 1 ሚሊየን 159 ሺህ 794 የፓስፖርት አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የፓስፖርት አሰጣጥ ተደራሽነትን ለማስፋት የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቁጥር ከ12 ወደ 22 ማደጉን አንስተው፤ በዓመቱ መጨረሻ ቁጥሩን 28 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ10 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ ተቋሙ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከተሰጡ አገልግሎቶች 30 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተገኝቷል ብለዋል።
በታምራት ደለሊ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.