መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት በአፍሪካ ፈርቀዳጅ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ የተመረቀው የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት በአፍሪካ ፈርቀዳጅ የሚባል ስራ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተንቀሳቃሽ አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ማንኛውም ሰው በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ሲያገኝ ለኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ እድገት ምስክርነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
እንደዚህ ያለ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጡ ስራዎች ለምናስበው የብልጽግና ጉዞ በጣም ወሳኝ ናቸው በማለት ገልጸው፤ አገልግሎት ከታነቀ ብልጽግናን ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል።
ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙበትን ጊዜ ማሳጠርና አገልግሎቱን አውቀው በቀላል መንገድ እንዲያገኙ እና ንግድ እንዲሳለጥ ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያና የአመራሮች መሰልጠን አሁን ጉዟችንን ጥሩ አድርጎታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሁሉም ዘርፎች ቴክኖሎጂን ያቀፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በተሟላ መንገድ ዜጎች ባሉበት ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
2 ሺህ የሚጠጉ አገልግሎቶች ከ45 ያላነሱ ማዕከሎች እንዲሁም ሞባይል አገልግሎት ማስፋት በምሳሌነት የሚጠቀስ አፈጻጸም መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከነበርንበት ባህል፣ ልምድና የአሰራር ዘዬ አንፃር ይህንን ማሳካት አስቸጋሪ ቢሆንም አሁን ያለው ሁኔታ በእጅጉ ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፍ የጀመርነውን አስደሳች፣ ተስፋ ሰጪ፣ አመርቂ እና ፈጣን ስራ በተሰናሰነ መንገድ የምንመራ ይሆናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ