በሀገር በቀል ሪፎርሞች ኢትዮጵያ ካቀረቀረችበት ቀና ብላ የብልጽግና ጉዞን በጽናት እያስቀጠለች ትገኛለች – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር በቀል ሪፎርሞች ኢትዮጵያ ካቀረቀረችበት ቀና ብላ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በጽናት እያስቀጠለች ትገኛለች አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ዛሬ የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛውን የ100 ቀን አፈጻጸም ሪፖርት ከፌዴራል ተቋማት አመራሮች ጋር መገምገም ጀምረናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ የሚገባትም ትልቅ ሥፍራ ነው፤ እኛ ደግሞ የዚህ ታሪክ ሰሪዎች የመሆን ዕድል በእጃችን ላይ ነው በማለት ገልጸው÷ ይህ መድረክ የኢትዮጵያን አዲስ ታሪክ የመጻፍ ሂደታችንን የምንገመግምበት፣ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ የምናስተሳስርበት ትልቅ መስታወት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ትናንት ያልተጠናቀቀ ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ የዴሞክራሲ እጦት፣ የአካባቢያዊነትና የሀገራዊነት ግጭት ይፈትኗት የነበረችው ኢትዮጵያ÷ ዛሬ በለውጡ አማካኝነት ሀገራዊ ምክክር የጀመረችበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ያደገበት፣ አሣሪ ሕጎች ተሻሽለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የጸደቀበትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የጠነከረበትን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ቀይሳለችም ነው ያሉት።
ከለውጡ በፊት ፕሮጀክቶች የብክነትና የመዘግየት ምልክቶች የነበሩበትን “እንደ መንግሥት ፕሮጀክት አቁሞ ያስቀራችሁ” የሚለውን መርገም ዛሬ በሥራ ዲሲፕሊንና በክትትል ሰብረነዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ፕሮጀክት መጀመር፣ በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ መለያችን ሆኗል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና በዲጂታል ኢትዮጵያ ዘርፍ የተካሄደው የመሠረተ ልማት አብዮት የሀገራችንን እንዲሁም የከተሞቻችንን ገጽታና አገልግሎት ቀይሯል ሲሉም አመላክተዋል።
በስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የተረጅነትን ቀንበር ሰብረን ወደ ምግብ ሉዓላዊነት እየተጓዝን ነው ብለዋል።
በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ ከርዳታ ጠባቂነት ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት በመሸጋገር በዓለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነቷን ወደ ላቀ ምዕራፍ አሳድጋለችም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
የዛሬው ትጋታችንም ለነገው ትውልድ አሻራችን ነው፤ ትልልቆቹን ፈተናዎች አሸንፈን፣ ታላላቆቹን ዕድሎች በመጠቀም በቁጭትና በሀገር ፍቅር መንፈስ የሚያስመሰግን ሥራ ዛሬ እንስራ ሲሉም አሳስበዋል።