ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ በወታደራዊ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ከሞዛምቢክ መከላከያ ሚኒስትር ኢ ክርስቲያቮ አርቱር ቹሜ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በወታደራዊ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በተለይም በፈረንጆቹ 2009 በሀገራቱ መካከል የተደረገውን ወታደራዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ የጋራ ጥምር ኮሜቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባት በሚቻልባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የሀገራቱ በትብብር መስራት የበለጠ አቅም ለማግኘትና በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ላይ ውጤት ለማምጣት እንደሚጠቅም ተመላክቷል፡፡
የዛሬው ምክክር ጥምር ኮሚቴውን ለማቋቋምም ሆነ የወደፊቱን ወታደራዊ ግንኙነትና ትብብር ለማስቀጠል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት መገለጹን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡