የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከኦፔክ አባልነት ራሷን አገለለች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከነዳጅ ላኪ ሀገራት ድርጅት (ኦፔክ) እና ኦፔክ ፕላስ አባልነት ራሷን አግልላች፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ የነዳጅ ባለፀጋዋ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በቀጣናው ጦርነት ምክንያት ዓለም በነዳጅ ዋጋ ግሽበት እየተፈተነ ባለበት ጊዜ ነው ከአባልነት መውጣቷን ያስታወቀችው፡፡
በዚህም መሰረት ሀገሪቷ ከፈረንጆቹ 2026 ግንቦት 1 ጀምሮ በይፋ ከኦፔክ ግሩፕ ጋር ትለያያለች ነው የተባለው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ መስተጓጎሉ ሀገሪቱ ከኦፔክ ግሩፕ ለመውጣቷ ምክንያት መሆኑን ገልጻለች።
ሀገሪቱ የነዳጅ ምርቷን ለሀገር ውስጥ ምርት ማዋል እንደምትፈልግም አስታውቃለች፡፡
ውሳኔው በሀገር ውስጥ የነዳጅ ምርት ትኩረት ለማድረግ እንዲሁም የተረጋጋ እና ዘላቂነት ያለው የነዳጅ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተነግሯል።
በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢራን ሚሳኤሎች እና የድሮኖች የጥቃት ዒላማ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ስትሆን በነዳጅ ማጣሪያዎቿ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮቿ በርካታ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡
እንደ አሜሪካ የንግድ አስተዳደር መረጃ ኦፔክ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ 10 የነዳጅ አምራች ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን በተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች 12 አባላት ያሉትን ኦፔክ ግሩፕ የተቀላቀለችው በፈረንጆቹ 1967 እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ