Fana: At a Speed of Life!

ድህነትን ታግሎ ማሸነፍ ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው – ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ድህነትና ኋላቀርነትን ታግሎ ማሸነፍና ለሀገር አንድነት ዘብ መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው አሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን።

85ኛው የአርበኞች በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት አደባባይ ተከብሯል።

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከ85 ዓመት በፊት የሕይወት መስዋዕትነትን የከፈሉ አርበኞች ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ነፃ ሀገር እንድንረከብ አድርገዋል።

ከ85 ዓመት በፊት ለአምስት ዓመታት መራራ የሆነ የግፍ ፅዋ ተጎንጭተው ሀገርን ለታደጉ አርበኞች ምስጋና፣ ፍቅርና አክብሮት ይገባል ብለዋል።

ዛሬም ሀገሪቱ ድህነትንና ኋላቀርነትን ታግለው የሚያሸንፉ፣ ለልማት እንዲሁም ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ፍቅር ዘብ የሚቆሙ አርበኞች እንደሚያስፈልጋት አንስተዋል።

በሀገሪቱ ታሪክ አዲስ የሆነው ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችለውን ሀገራዊ ምክክር መድረክ ይዞ የመጣውን እድል መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።

ፍትሃዊ ባልሆነ አግባብ ያጣነውን ባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የህልውናና የመብት ጉዳይ መሆኑን መረዳት እንደሚገባም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በበዓሉ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ አባትና እናት አርበኞች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.