የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ኮንፍረንስ አጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 21 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ለ ሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ኮንፍረንስ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀቀ።
የሀረሪ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ጽህፈት ቤት ሃላፊና የርእዮተ አለምና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብዱልሃኪም ኡመር ÷ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተደረገው የውይይት መድረክ ያለፉትን ሁለት አመታት የስራ ሂደት የተገመገመበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ግምገማ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀጣይ ሊሰሩ የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡንም ተናግረዋል።
በኮንፈረንሱ በክልሉ ቀድሞ ሃብሊና ኦዲፒ በሚል መጠሪያ
የሚታወቁትን ሁለቱን ፓርቲዎች በማዋሃድ በጋራ ያጣመረና በብልፅግና ፓርቲ አንድ ያደረገ መሆኑንም ተገልጿል።
ይህም ቀድሞ የነበሩትን አስተሳሰቦች አራግፎ በመጣልና የቀጣዩን የብልጽግና አስተሳሰብ በመላበስ ለቀጣዩ የብልጽግና ጉዞ ዝግጅት ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ ከብልጽግና ፓርቲ አስተሳሰብ መርሆችና እሴቶች አንጻር ያልጠሩ የነበሩ የአመለካከት ችግሮችን ከማጥራት አንጻር የተፈተሸበትና የተገመገመበት የውይይት መድረክ መሆኑንም አቶ አብዱልሃኪም ኡመር ተናግረዋል።
የአቋም መግለጫውን ያቀረቡት አቶ አሚር አቂል በበኩላቸው÷የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ኮንፍረንስ በሃገሪቱ የተጀመረውን ለውጥና ትሩፋቶች ያስገኛቸውን ድሎችና ያጋጠሙ ፈተናዎች ላይ ሰፊ የሃሳብ ልውውጥና ውይይቶች መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ ሰላም መስፈን፣የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ለህዝብ ህልውናና ለብልጽግና እውን መሆን የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
በክልሉ የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፣ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ የሴቶችን ተጠቃሚነትና የወጣቱን የስራ እድል ፈጠራ እውን ለማድረግ ብሎም ብልሹ አሰራርን በማስወገድና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከጋራ መግባባት ላይ መደረሱን እና ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።