Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከ330 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስንዴ በማምረት ከአፍሪካ አንደኛ ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘንድሮ ኢትዮጵያ ከ330 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስንዴ በማምረት ከአፍሪካ አንደኛ ናት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱልልታ ወረዳ በ2 ሺህ 150 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ማሳን ዛሬ ከጎበኙ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ÷ በግብርና ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች እያስገኙት ያለው ውጤት በእጅጉ የሚያስደምም ነው፡፡

ስኬቱም ይበልጥ እንድንበረታና እንድንተጋ እንዲሁም አዳዲስ ሃሳቦችን እንድንፈጥርና እንድንሞክር ጉልበት የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

ኮቪድ-19 እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የበጋ እርሻ እና የበጋ ስንዴ በኢትዮጵያ የተለመደ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡

የበጋ እርሻ መሬት ጦም ማደር የለበትም፤ ከልመና መውጣት አለብን፤ ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬት አለን ከሚል ጽኑ እምነት መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

አሁን ላይም የበጋ ስንዴ ልማት ባስገኘው ውጤት ብዙሃኑን እያሳመነ አስደማሚ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው ያወሱት፡፡

ኢትዮጵያ ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት በፊት ስንዴን ከውጭ የምታስገባ ብቻ ሳይሆን አነስተኛ ምርት ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትመደብ ነበረች ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በዘርፉ አስደማሚ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመው÷ ዘንድሮ ባለፈው ክረምት ብቻ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር እንዲሁም በበጋ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ገደማ መሬት መታረሱን ገልጸዋል፡፡

በድምሩ 8 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መታረሱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ከዚህም ከ330 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያን በስንዴ ማምረት ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል ነው ያሉት፡፡

አምና ከታረሰው መሬት ዘንድሮ 950 ሺህ ሄክታር ገደማ ጭማሪ አሳይቷል፤ ባለፈው ዓመት ክረምት እና በጋ 280 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ መመረቱን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት ደግሞ 331 ሚሊየን ኩንታል ተመርቷል፤ በዚህም በአንድ ዓመት የ50 ሚሊየን ኩንታል ጭማሪ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.