Fana: At a Speed of Life!

የተቋማት ግንባታ ለሀገር ልዕልና…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንድ ሀገር ጠንካራ እና ተከታታይነት ያለውን ዕድገት ማስመዝገብ የሚችለው ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ እንደሆነ እሙን ነው።

በዚህም ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ምሰሶ በመሆን የዜጎች እኩልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።

በተለይም የፀጥታ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም ለዚህ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚሁም ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል መሰረት መጣል ተችሏል።

ተቋማቱ በአመራርና በሰው ኃይል የተጠናከሩ፣ አቅማቸው በቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ በደኅንነት መሰረታዊና አንኳር ክህሎቶች የፈረጠሙ እና በዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ የታነፁ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።

በውጤቱም ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ፣ ወገንተኝነታቸው ለህግ ብቻ የሆኑ፣ ጠላቶች ኢትዮጵያ ላይ ፈፅሞ ክፉ እንዳያስቡ የሚያደርጉ፣ ለሀገር ጋሻ እና ጥላ የሆኑ ተቋማት ተገንብተዋል።

በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች በዘርፉ የሚስተዋሉ ስጋቶችን ከመቀልበስ ባሻገር ቀድሞ ችግሮችን በመለየትና አዝማሚያዎችን በመተንተን ድንገተኛ የሚባሉ የደኅንነትና የፀጥታ ክፍተቶችን ማስቀረት እየተቻለም ይገኛል።

በተጨማሪም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በተደረገው ሪፎርም ውትድርና ጀግኖች የሚመርጡት ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት ዋጋ የሚከፈልበት የተከበረ ሙያ መሆን ችሏል።

በዚህም ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ ትጥቅን በማሟላት የሀገርን ተጋላጭነት ማስቀረት የሚችል አስተማማኝ ኃይል ማድረግ ተችሏል።

ለዚህም የሆሚቾ ጥይት ፋብሪካ እና የድሮን ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርተው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ በመገንባት ስራ መጀመራቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዘመኑ ጋር መጓዝ እንድትችል መንግሥት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ የሚገኝ ዘርፍ ሲሆን÷ የሰዎችን ህይወት ቀላል በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ለተለያዩ ዓለማ በመዋል ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያም የዘርፉን ሚና በመገንዘብ ተቋም በመገንባት “ኤአይ ለሁሉም” በሚል መሪ ሐሳብ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ከጫፍ ደርሳለች።

በተጨማሪም መንግሥት በጸጥታ አካላት፣ በሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በፍትሕ አካላትና በሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ሪፎርም ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.