በ1 ሺህ 234 ወረዳዎች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ ተከናውኗል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ1 ሺህ 234 ወረዳዎች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ ተከናውኗል አለ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የምክክር ኮሚሽኑን የእስካሁን ተግባራትና ቀጣይ አቅጣጫ የሚገመግም መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ሀገራዊ ኮሚሽኑ የአፈፃፀም ሪፖርቱን ዛሬ ጠዋት ላይ አቅርቧል።
እስካሁን ያከናወናቸውን ዐበይት ተግባራት፣ የገጠሙትን ተግዳሮቶች እና ለተግዳሮቶቹ የሰጣቸውን መፍትሔዎች እንዲሁም ወደፊት የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በታሰበው ልክ ለማስኬድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ሚናዎችን አስቀምጧል።
አካታች እና አሳታፊ የሆነ የምክክር ተሳታፊዎች መለየት እና የኢትዮጵያን 93 በመቶ የሸፈነ በ1 ሺህ 234 ወረዳዎች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ በማድረግ ቁልፍ ስኬት አስመዝግቧል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ 22 ዙር የሚሆን ከተለያዩ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመመካከር የተደረገበት ሰፊ ጥረት ቢኖርም ባለው ምቹ ያልሆነ ሁኔታ በትግራይ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ምክክር ለማድረግ አለመቻሉን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
ለዚህ ተግዳሮት ምላሽ ለመስጠትም ከመላው የትግራይ ክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆችን በማካተት በአዲስ አበባ ከተማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ ማካሄዱን ጠቅሷል።
በቀጣዩ የሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ ኮሚሽኑ የፖለቲካ ተዋንያንን ተሳትፎ ማጠናከር እና የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን መቅረፅ ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቁሟል።
እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤን ማካሄድ እና በሀገር ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን ውጤቶች እና ምክረ ሀሳቦች ተፈፃሚነት ማመቻቸት የሚሉት የኮሚሽኑ ቀጣይ ስራዎች ውስጥ እንደሚገኙበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።