Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብ ጥያቄ የነበረው የመሰረተ ልማት ፍትሐዊ ተደራሽነት ላይ ውጤት እየተመዘገበ ነው – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የነበረውን ፍትሐዊ ያልሆነ የመሰረተ ልማት ስርጭት ለማስተካከል ባለፉት አራት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።

ሚኒስትሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ከለውጡ በፊት የመሰረተ ልማት ፍትሐዊ ተደራሽነት ላይ ከሕዝብ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር።

ለአብነትም በአንዳንድ ክልሎች የውሃ ሽፋን 38 በመቶ ብቻ ሲሆን በሌሎች ደግሞ እስከ 70 በመቶ የሚደርስበት ኢፍትሐዊ ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከለውጡ መንግሥት በኋላ የልማት ሥራዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

በተለይ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በቦረና ዞን ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን አንስተዋል።

እነዚህ አካባቢዎች የውሃ ሀብታቸውን በመጠቀም ወደ መስኖ ልማትና የስንዴ ምርት መሸጋገር መቻላቸውን ጠቁመዋል።

በቦረና ዞን አርብቶ አደሩ ወደ አርሶ አደርነት እየተቀየረ መሆኑን፣ በአፋር ክልል የተንዳሆ ግድብን በመጠቀም ሰፊ የመኖ ልማት መጀመሩን እና በሶማሌ ክልል በብዛት ስንዴ እየተመረተ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦትም በእጥፍ ማደጉን አንስተዋል።

ቀደም ሲል ከ4 ሺህ ሜጋ ዋት ያልበለጠው የሀገሪቱ የኃይል ማመንጨት አቅም አሁን ላይ ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት እየተጠጋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ይህም ለከተሞች ውበትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የኃይልና የመሰረተ ልማት እድገቱ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን እንድታስተናግድ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.