Fana: At a Speed of Life!

እስራኤል በኢትዮጵያ የምታደርገውን ኢንቨስትመንት አጠናክራ ትቀጥላለች – አምባሳደር አብረሃም ንጉሴ (ዶ/ር)

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤል በኢትዮጵያ የምታደርገውን ኢንቨስትመንትና የልማት ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች አሉ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብረሃም ንጉሴ (ዶ/ር)፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የመስክ ጉብኝት እያደረጉ ነው።

አምባሳደር አብረሃም ንጉሴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ነው።

በተለይም በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በፈጠራ ስራዎች እና በሰው ኃይል ልማት ዙሪያ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ከግብርናና የንግድ ትስስሮች በተጨማሪ በሳይበር ደህንነት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ የህክምና መሠረተ ልማት ዙሪያ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የእስራኤል የቴክኖሎጂ ተቋማት የኢትዮጵያን ዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ማህበረሰቦች ለኢኮኖሚና የዲፕሎማሲዊ ትስስር መጠናከር ትልቅ ምሰሶ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዮሐንስ ፋንታ በበኩላቸው÷ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ያገኘውን ተጨባጭ መረጃ መነሻ በማድረግ የሀገራቸውን ታዋቂ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ እንዲሰማሩ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥትም ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.