Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት አከናውናለች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት አከናውናለች አለ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ፡፡

”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የኢኮኖሚ ትንተና ቢሮ ኃላፊ አባስ መሐመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የስታስቲክስ ልማት ፕሮግራም ቀርጻ ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

በዚህም ባለፉት 8 ዓመታት ተግባራዊ የሆኑ የ10 ዓመት የልማት እቅድ እንዲሁም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በርካታ ዓላማዎችና ግቦችን በውስጡ ይዞ የተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እነዚህ ፕሮግራሞችና እቅዶች ተግባራዊ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ መረጃና ማስረጃ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፥ የመረጃ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አንጻር በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

መረጃና ማስረጃ የሌለው ግብ ምኞት ከመሆን የተሻገረ አይሆንም ያሉት ኃላፊው፥ በዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዚያት የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ልማት ፕሮግራም ቀርጻ ተግባራዊ አድርጋለች ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ በዋናነት የዓለም አቀፍና የሀገራዊ ስታንዳርዶችን መሰረት ያደረገ ሲሆን፥ በሀገሪቱ ያሉ የመረጃ ክፍተቶችን ከመሙላት ባሻገር መረጃ የሚመነጭበት መንገድ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የሚያደርግ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የመረጃ ሉዓላዊነት የአንድን ሀገር ህዝብን የመቁጠር፣ ኢኮኖሚን የመለካት እና የተሰበሰበ መረጃን የመጠበቅና ለሀገር ጥቅም የማዋል መብትን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.