እውነትን የመግለጽ እና ብሔራዊ ጥቅምን ማስገንዘብ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እውነትን የመግለጽ እና ብሔራዊ ጥቅምን ማስገንዘብ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
አገልግሎቱ ያወጣው መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
መገናኛ ብዙኃን የዲሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ አስቻይ መሠረተ ልማት ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃን በሚዛናዊነት እና ገለልተኛነት የማገልገል ኃላፊነት ያለባቸዉ የዴሞክራሲ ተቋማት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን መርሕ በሕገ መንግሥቷ ያረጋገጠች ሀገር ናት፡፡
ይህ ማለት ግን መገናኛ ብዙኃን የሚሠሩበት ሀገር እና የሚያገለግሉት ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም አይመለከታቸዉም ማለት አይደለም፡፡ ገለልተኛነታቸዉ ሕጋዊ አሠራርን ከመጠበቅ፣ ለአንድ ቡድን ወይም አካል የተለየ ውግንና አለማሳየት፣ ከእውነት ጋር መቆም ማለት ነው፡፡
ገለልተኛነታቸዉ የሚረጋገጠዉም አንድን እውነት መታየት ከሚገባዉ አንጻር በማየትና በመፈተሽ ሲገለጽ ነው፡፡
መገናኛ ብዙኃን እውነትን የመግለጽ እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስገንዘብ ኃላፊት አለባቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች አንዱ መሠረት ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዐት የሚገነባበት፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት፣ የመንግሥት እና ሕዝብ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ጥልቅ መሠረት የሚይዝበት በመኾኑ መገናኛ ብዙኃን ይህንኑ ታሳቢ አድርገዉ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ምርጫ ከኢትዮጵያ ሕግ፣ ሕጋዊ ተቋማት እና አሠራር አንጻር ማየት እና ማሳየትም አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የሥነ መንግሥት ታሪክ እና ባህል አላት፡፡ ነገር ግን በዚያ ልክ ራሷን አልገለጸችም፤ መገናኛ ብዙኃኗም በበቂ አልገለጿትም፡፡ በዚህ ምክንያት ዓለም የራሱን መረዳት ተጠቅሞ ያለመገለጫዋ ሲገልጻት ኖሯል፡፡ ዛሬ ላይ ገና ማደግ የሚገባቸዉ ቢኾኑም በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አሉን፡፡ ከድሮ በተሻለ ኢትዮጵያን የመግለጽና ተፅዕኖ የመፍጠር ዐቅምም አዳብረዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ የምንገነባ፣ አፍሪካዊ ሥነ መንግሥት የምናጸና መኾናችንን በእውነታዉ ላይ ተመርኩዘዉ የመግለጽ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ 7ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ቀናት ቀርተዋታል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ከተገነዘቡት ተቋማዊ የማስፈጸም ዐቅም እና የዴሞክራሲ ልምምድ ተነሥተዉ በድምፃቸዉ መንግሥታቸዉን ለመምረጥ በነቂስ ተመዝግበዋል፡፡
ለምርጫዉ ከ52 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ካርድ ወስደዋል፡፡ ይህም በዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገ ከፍተኛ የሕዝብ ቊጥር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገራቸዉን ቢመራ የበለጠ ወደ ከፍታ የሚያሸጋግራትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸዉን ቅድመ ዝግጅትም እያደረጉ ነው፡፡
በዜጎች የመምረጥ ውሳኔ ላይ መገናኛ ብዙኃን ያላቸዉ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ አማራጭ ሐሳቦችን ለሕዝቡ በማድረስ ረገድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመደበዉ የአየር ሰዓት ድልድል ባሻገር ተጨማሪ ዕድሎችን በማመቻቸት ሕዝቡ በቂ መረጃ እንዲያገኝ መገናኛ ብዙኃኑ በትኩረት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሕዝቡን ይሁንታ ያስገኝልናል ያሉትን አማራጭ ሐሳብ እያንሸራሸሩ ነው፡፡ ይህንን የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ልምምድ አጉልቶ ማሳየት የመገናኛ ብዙኃኑ ተፈጥሯዊ ተግባር ነው፡፡
የምርጫ ወቅት ሐሰተኛ መረጃ እንደ አሸን የሚፈላበት እና ሕዝብ ላይ ብዥታ የሚፈጥርበት ወቅት ነው፡፡ የውስጥ ባንዳዎች እና ባዕዳን ተቀናጅተዉ ኢትዮጵያን ጥላሸት ለመቀባት የሚታትሩበት ጊዜ ላይም እንገኛለን፡፡ በእንዲህ ያለዉ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች እውነቱን የማስገንዘብ፣ ሐሰቱን የማጋለጥ ኃላፊነታቸዉን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ መንግሥትም ሕዝብም ይጠብቃሉ፡፡