የኢትዮጵያን ሕዝብ በትናንሽ ፕሮፓጋንዳ ሸብረክ ማድረግ አይቻልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ሥርዓትና መንግሥት የምታውቅ ጥንታዊ ሀገር ሕዝብን በትናንሽ ፕሮፓጋንዳ ሸብረክ ማድረግ አይቻልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት÷ የሀገሪቱ ሕዝብ ከጠዋት ጀምሮ ሰልፍ በመያዝ እያሳየ የሚገኘው ከፍተኛ የጀግንነት መንፈስ የሚደነቅ ነው።
ሕዝቡ እያደረገ ያለው ይህ ርምጃ የዴሞክራሲ ሥርዓትና ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው÷ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ውሳኔ ለመወሰን መካሪና ገሳጭ እንደማያስፈልገው በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ በቁርጠኝነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመርጣቸው አካላት የታላቁን ሕዝብ እምነት ሳይክዱ ታምነው፣ እጃቸውና ልባቸው ንጹሕ ሆኖ፣ ደከመን ታከተን ሳይሉ ታሪክ ለመቀየር ምን ያህል ዝግጁ ናቸው የሚለው ጉዳይ ዋነኛው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ውድድሩ ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ሳይሆን ራሱን አሳልፎ የሰጠንን የታመነ ሕዝብ አገልግሎትና ሕይወት እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚለው መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እስካሁን ከተሠራው በላይ መልካም ሥራን፣ ልፋትን፣ ማሰብንና መደመርን ይጠይቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሥርዓትና መንግሥት የምታውቅ ጥንታዊ ሀገር እንደሆነች እና ሕዝቡን በትናንሽ ፕሮፓጋንዳ ሸብረክ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸው÷ ታላቅነቱን አክብሮ፣ ሕይወቱን ቀይሮ ማለፍ ለሁሉም ወገን አሸናፊነትን እንደሚያመጣ አስረድተዋል።
የሚመጣውን ማንኛውንም የሕዝብ ውሳኔ ውጤት በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በምርጫው ያሸነፉ አካላት በታማኝነት እንዲያገለግሉ፣ የተሸነፉት ደግሞ ውጤቱን በፀጋ እንዲቀበሉ አስገንዝበዋል።
በዮናስ ጌትነት