በዓለም ዋንጫ የተለያዩ ሀገራትን የወከሉት አባትና ልጅ…
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ልጅ ሉካ ዚዳን አልጄሪያን በመወከል በሰሜን አሜሪካ ሀገራት በሚሰናደው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ይሳተፋል፡፡
ከዚህ ቀደም አባቱ ዚነዲን ዚዳን ከፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመድረኩ ወርቃማ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡
ዚዳን የሚለው ስም በእግር ኳሱ ዓለም እንዲናኝ ያደረገው ዚነዲን ዚዳን በፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን እጅግ የተሳካ ጊዜ ስለነበረው ነው፡፡
ሀገሩ ለመጀመሪያ ጊዜ አሰናድታ ሻምፒዮን በሆነችበት የ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ኮከብ ከመሆኑም ባለፈ በ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ የፍፃሜ ተፋላሚ ነበር።
በእግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ዚነዲን ዚዳን ልጅ ሉካ ዚዳን በአንጻሩ ከፈረንሳይ ይልቅ ለአያቶቹ ሀገር አልጄሪያ መጫወትን መርጧል፡፡
ሉካ ዚዳን በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው አለም ዋንጫ የበረሃ ቀበሮዎቹ ግብ ጠባቂ በመሆን እንደ አባቱ በዓለም ዋንጫው ተሳትፎ ያደርጋል፡፡
በሙባረክ ፈንታው