Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በኢራን ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተሯ በኢራን ድሮን መመታቱን ተከትሎ በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ በሚገኙ የኢራን የአየር መከላከያ እና የራዳር ጣቢያዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት ፈጽማለች።

ጥቃቱ በባሕረ ሰላጤው ላይ ለተመታችው የአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተር የተመጣጠነ ምላሽ መሆኑንም ገልጻለች።

የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ የሚገኙ የኢራን የአየር መከላከያ፣ የምድር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች እና ራዳሮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው የገለጸው።

ኢራን ለሄሊኮፕተሯ መውደቅ ኃላፊነት ባትወስድም ለአሜሪካው ድብደባ ምላሽ ለመስጠት በባህሬን እና ዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የሮኬት ጥቃት መሰንዘሯን ገልጻለች።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በባህሬን እና ዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ውስጥ ባለ 21 ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጥቃቱ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ዋሽንግተን እና ቴህራን የቀጣናውን ጦርነት ለማቆም ድርድር ላይ በመሆናቸው ሁለቱም ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ አሜሪካ ጥቃት መፈጸሟን እንድታቆም አስጠንቅቀዋል።

የውጭ ኃይሎች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ከፈለጉ ቀጣናውን ለቀው መውጣት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አጽንዖት መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.