Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደስታ ሌዳሞ በ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን መርቀው ስራ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡

ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት ፕሮጀክቶች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ ዘመናዊ ማዕከላዊ የቀዶ ሕክምና ማዕከል፣ ልዩ የቀዶ ጥገናና የጽንስ ሕክምና ከፍተኛ እንክብካቤ፣ የጡት ወተት ባንክ፣ የክሊኒካል ሙከራ ዩኒት ይገኙበታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው አበረታችና ወጪ ቆጣቢ ውጤት የተቋሙን ትልቅ አቅም የሚያሳይ ነው፡፡

ፕሮጀክቶቹ የጤና አገልግሎትን ለማስፋፋት፣ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅና ጥራት ያለው ሕክምና ለማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለሕዝቡ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የጤና ሥርዓቱ ከሕክምና አገልግሎት ባሻገር በመከላከል፣ በምርምር፣ በእናቶችና ሕጻናት ጤና እንዲሁም በአካባቢ ጤና ጥበቃ ዘርፎች ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ፕሮጀክቶቹ የህክምና አገልግሎትን፣ የህክምና ትምህርትና የጤና ምርምርን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.