Fana: At a Speed of Life!

‎ሰራዊቱ የማይወዛወዝ ምሰሶ በመሆን ሀገር የማሻገር ተልዕኮውን እየተወጣ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መከላከያ ሰራዊቱ ‎የማይወዛወዝ ምሰሶ በመሆን ሀገር የማሻገር ተልዕኮውን እየተወጣ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፡፡

‎ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በማዕከላዊ ዕዝ መኮንኖች የግዳጅ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች መድረክ ላይ በበይነመረብ የማጠቃለያ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የተዘጋጀና የተሾመ ወታደራዊ አመራር ዓለም አቀፉዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በመረዳት የሚመራውን አሀድ ስነ ልቦናዊ ዝግጁነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

‎ወታደራዊ መኮንኖች የጦሩን የዕለት ተዕለት ውስጣዊ አቅሞች በመፈተሽ ድል የሚፈጥርና ኃላፊነት የሚጣልበት የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ገልጸው፥ ሀገር እና ተቋም የሚረከበው ተተኪ መኮንን አመርቂ ግዳጅ እየፈፀመ ይገኛል ብለዋል።

‎የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የድል አድራጊነቱ ምስጢር ወታደራዊ ስነምግባርን የተላበሰ መሆኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፥ ሰራዊቱ የማይወዛወዝ ምሰሶ በመሆን ሀገር የማሻገር ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‎የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ በበኩላቸው፥ ተቋሙ በተለያዩ መስኮች የሚያሰለጥናቸው መስመራዊ መኮንኖች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚግባቡ በመሆናቸው ተልዕኮን በአጭር ጊዜና አነስተኛ ኪሳራ የመፈፀም ብቃታቸው ከፍ ማለቱን አንስተዋል፡፡

ዕዙ ለማንኛውም ስምሪት አጋዥ የሆኑ የሰራዊት ግንባታ አቅጣጫዎችን በመጠቀም ለድል አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.