የገዳ ሥርዓት የሕዝቡን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርጽ በመሆኑ እንዲጠበቅ ይሰራል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገዳ ሥርዓት የዛሬውን ህያው ማህበራዊ ህይወትና የሕዝቡን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርጽ በመሆኑ ይበልጥ እንዲበለጽግና እንዲጠበቅ በትኩረት ይሰራል አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
71ኛው የቱለማ ኦሮሞ ገዳ የስልጣን ርክክብ በሸገር ከተማ ዳካ ኮራ አርዳ ጂላ በድምቀት ተካሂዷል።
በዚህም መሠረት የሜልባ አባ ገዳ ጎበና ሆላ የስልጣን ዘመናቸውን አጠናቀው ለሙደና አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።
ከቀናት በፊት በዳካ ኮራ የተሰባሰቡ አባ ገዳዎችና በተለያዩ የገዳ ሥርዓት እርከኖች ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
በየስምንት ዓመቱ በሚካሄደው የገዳ የስልጣን ሽግግር ደንብ መሠረት ዛሬ ከገዳ ሜልባ ወደ ገዳ ሙደና የአለንጌ ሽግግር ተደርጓል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ዋነኛ መሠረት በመሆኑ እሴቶቹን ይበልጥ ማጠናከርና ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ባከናወነው የባህል ሕዳሴ ከዚህ ቀደም ተረስተውና ተጥለው የነበሩ የኦሮሞ ባህሎችና እሴቶች ዳግም እንዲያንሰራሩና እንዲገነቡ አድርጓል ብለዋል።
ይህንኑ ለማሳካትም ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ የገዳ ሥርዓት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ መደረጉንና ትውልዱን በገዳ ሥርዓት እሴቶች ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ከሰጣቸው ቀዳሚ ትኩረቶች መካከል አንዱ የኦሮሞን ሕዝብ ጥንታዊ ባህል፣ እሴትና ማንነት ማልማት እንዲሁም ጠንካራ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት መሆኑንም አመልክተዋል።
ይህን ጥንታዊ እውቀት ማስቀጠል፣ ታሪካዊ ትረካዎችን ማስተካከል፣ እሴቶቹን ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለኪነጥበብ፣ ለሚዲያ፣ ለስነ-ጽሁፍና ለእውቀት ምንጭነት ማዋል እንዲሁም ራሱን የቻለና ከተጨባጩ የዓለም ሁኔታ ጋር የተላመደ ትውልድ መፍጠር የክልሉ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚህ የቱለማ ገዳ የአላንጌ (የስልጣን ሽግግር) ባህላዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሳዳ አብዱራህማን፣ የሸገር ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ አባላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።