ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀድሞ የሕወሓት ቡድንን ጸረ ሰላም እንቅስቃሴ ሊያወግዝ ይገባል- ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ ሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ ያለግጭትና ብጥብጥ እንደማይኖር ያሳያል አሉ የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር)።
ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር) ÷የተለያዩ ሀገራት መንግሥታት፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና የልማት አጋሮች የትግራይ ክልልን የሰላም ሂደት በሚያደናቅፈው የሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን ላይ ግልጽና ጠንካራ አቋም እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማስጠበቅ ያሳየው ከፍተኛ ትዕግስት የሚደነቅ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን የፌዴራል መንግሥት በመልሶ ግንባታና በፖለቲካ አስተዳደር የሰላም ስምምነቱን ለማስከበር ያደረገውን ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደናቅፍ መቆየቱን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅትም የትግራይ ክልል ህዝብ የዳግም ጦርነት ሙከራን አጥብቆ እየተቃወመ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን ክልሉን ወደ ዳግም ጦርነት ለማስገባት እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት በመፈፀም ያለግጭት እንደማይኖር ሕገ-ወጥነቱን በተግባር እንዳሳየ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በማካሄድ በወጣቶች ላይ የከፋ እንግልት እየፈጸመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ያልተፈቱ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮችም በውይይት፣ ሕገ-መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ በወታደራዊ አካሄድ እንደማይፈቱም አስገንዝበዋል።
የትግራይ ክልል ከዓመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከደረሰበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና ሳያገግም ሌላ ግጭት መሸከም እንደማይችል ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ባንዳና የውጭ ባዕዳን ጸረ-ሰላም ኃይሎችም የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ”ጽምዶ” በሚል ጥምረት የክህደት እንቅስቃሴ እያዳረጉ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህ የጥፋት እንቅስቃሴም ቀጣናዊ የሰላም መናጋትን የሚያስከትል በመሆኑ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር ሊወገዝ እንደሚገባ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለዚህም መንግሥታት፣ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሰላም ሂደት ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማውገዝና ጠንካራ አቋም መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት።