Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር መመለስ ለአፍሪካ ቀንድ ሁለንተናዊ ትብብር…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር መመለስ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴዔታ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር)፡፡

ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቅድሚያ የሚሰጠው የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው።

ጥያቄው በሁሉም መመዘኛ ተገቢ መሆኑን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለማንሳት ጠንካራ የታሪክና የሕግ መሰረት እንዳላት አመልክተዋል።

ይህ የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች የባሕር በር ጥያቄ ፍትሃዊና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በሰፊው የማስገንዘብ ሥራ ማከናወኗን ገልጸዋል።

በዚህም ጥያቄው በዓለም አቀፍ መድረክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እውቅና እያገኘ መምጣቱን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ ትስስርን እና መረጋጋትን በመምራት ረገድ ታሪካዊ ሚና ያላት ሀገር መሆኑን የገለጹት ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር መመለስ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

የቀጣናው ሀገራት ትስስርን በማጠናከር ረገድም የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር መመለስ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠላም ለጎረቤት ሀገራት ሰላም እውን መሆን ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው÷ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታ መሠረታዊ በሆነ መልኩ በማረጋጋት ቀጣናዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.