Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት በተከተለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳዑዲ አረቢያ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀምረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እንዳሉት፤ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህን በመከተል በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በሳዑዲ ሪያድ የሚገኘውን የኢፌዲሪ ሚሲዮንና ጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽህፈት ቤት በማስተባበር በተደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1 ሺህ 665 ዜጎች የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲሰጣቸው መደረጉ ይታወቃል።
መንግሥት ምህረት የተደረገላቸውን ዜጎች ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራን ዛሬ በይፋ መጀመሩን ገልጸው፤ ምህረት ከተደረገላቸው መካከል 340 የሚሆኑት ዛሬ ወደ ሀገራቸው ገብተዋል ብለዋል።
የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህን በመከተል መንግሥት በውጭ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አሁን የተገኘው ውጤት ላለፉት ሁለት እና ከዚያ በላይ ዓመታት ሲደረግ የቆየው ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ክትትል ፍሬ ነው ብለዋል።
ወደ ሀገር ከተመለሱት ዜጎች መካከል አብዛኛው በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉ ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሰው ሀገር ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉት በተሳሳተ መረጃ እና በተለያዩ ምክንያቶች ህገ ወጥ መንገድን በመምረጣቸው እንደሆነ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.