Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ማከናወን ትችላለች…

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ውስብስብ ፈተናዎች በራሷ አቅምና በሀገር በቀል ዕውቀት በመፍታት፣ ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ መሻገር እንደምትችል በየጊዜው ለዓለም እያሳየች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ማከናወን እንደምትችል ባለፉት ዓመታት የጀመረቻቸውን መዋቅራዊና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ወደ ተጨባጭና ዘላቂ ስኬት በማሸጋገር አስመስክራለች፡፡

ታከናውናለች የሚለው መሪ ቃልም ተራ የፖለቲካ መፈክር ሳይሆን፣ በተጨባጭ መሬት ላይ በወረዱ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና በማክሮ-ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጦች የተረጋገጠ ሀገራዊ እውነታ ነው።

ኢትዮጵያ በውስጣዊና ቀጣናዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና፣ በተጠናና የተቀናጀ አመራር ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ችላለች፤ ይህንንም መላው ዓለም መስክሯል፡፡

ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው እድገቶች የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል የመወሰን አቅም አላቸው፡፡ በተለይም የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት እና የካፒታል ገበያ መነቃቃት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የታላላቅ መሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ትስስር እና የአካታችነት ፍኖተ-ካርታ ከብዙዎቹ ዋና ዋናዎቹን እንደ መጥቀስ ነው፡፡

በማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት እና የካፒታል ገበያ መነቃቃት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት ከባህላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊና ገበያ መር መዋቅር ቀይሮታል።

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ላይ ማሻሻያ በማድረግ አሰራሯን ወደ ገበያ መር አሸጋግራለች፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት የጥቁር ገበያን ኢኮኖሚያዊ ጫና ከመቀነሱም በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የሬሚታንስ ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

የሰነደ መዋዕለ ንዋይ የካፒታል ገበያን በይፋ ሥራ በማስጀመሯ፣ መንግሥታዊና የግል ኩባንያዎች አክሲዮኖችን በመሸጥ የረጅም ጊዜ የሀገር ውስጥ ካፒታል የሚያሰባስቡበትና ዜጎች የባለቤትነት ድርሻ የሚገዙበትን አዲስ በር ከፍቷል።

በኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ አማካኝነት የሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያንሰራራ፣ የወጪ ምርት በሀገር ውስጥ እንዲተካ አድርጓል። በዚህም መዋቅራዊ ችግር የነበረባቸው 37 ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን፣ 1.08 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ከሀገር እንዳይወጣ ማዳን ተችሏል።

በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥታዊ አገልግሎት በዘመናዊ መንገድ በአንድ ማዕከል እንዲሰጥ አድርጓል፡፡

የመሶብ መተግበሪያ በአንድ ዲጂታል መስኮት ከ185 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን ያጠቃለለ ሲሆን፣ የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ረገድ አስደናቂ ለውጥ አምጥቷል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን አሠራር ግልጽነትና ቀልጣፋነት በማሳደግ ኢትዮጵያ የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙስና አዝማሚያዎችን በቴክኖሎጂ ለመግታት ትልቅ ምዕራፍ ተሻግራለች።

የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተመዘገቡበት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከባንክ ሥርዓት፣ ከፓስፖርት እና ከሲቪል ምዝገባ አገልግሎቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ተሳስሮ ሕጋዊና አስተማማኝ የቁጥጥር ሥርዓት ፈጥሯል።

በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ በብሔራዊ የኮዲንግ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ስልጠና ወስደው ለሀገራዊ ልማት የዕውቀት መሠረት እየሆኑ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የመሠረተ ልማቶች ግንባታ የአካባቢ ጥበቃን እና የዜጎችን የኑሮ ጥራት ያማከሉ ናቸው። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ምልክት ሆኗል፡፡ ግድቡ የኃይል ማመንጨት አቅምን በማጎልበት የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት በመሸጥ ቀጣናዊ ትስስርን አጠናክሯል።

በአዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የተከናወነው ፈጣንና ጥራት ያለው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ፅዱ እና ለዓለም አቀፍ ቱሪዝም ሳቢ አድርጓል።

ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ትልቅ አቅም ሆኗል። ከዚህ ጎን ለጎን የአየር ብክለትን ለመከላከል ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ሽግግር በከፍተኛ ፍጥነት እየተተገበረ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ስደተኞችን ሰብአዊ መብት በመጠበቅና ከሀገር ውስጥ ማኅበረሰብ ጋር በማዋሃድ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ጀምራለች። በቅርቡ ይፋ የሆነው የማካተት ፍኖተ-ካርታ ስደተኞችን በረድኤት ብቻ ከመደገፍ ወጥቶ በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ውስጥ በማካተት፣ የሥራ ፈቃድና የትምህርት ዕድል አግኝተው በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ስትራቴጂ ይፋ አድርጋ እየተገበረች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያን ፈተናዎች አያንበረክኳትም፡፡ በብልህ መሪዎቿ ታግዛ ፈተናዎችን ወደ ዕድል የመቀየር ልምድ አካብታለች፡፡ ወደ ሩቅ ከማማተር የውስጧን መፈተሸ ጀምራለች፡፡ በራሷ አቅምና በሀገር በቀል ዕውቀቶች ማከናወን እንደምትችልም እያሳየች ነው፡፡ ጉዞው ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ መሻገር እንደምትችል ሙሉ ተስፋን የሰጠ ነው።

ኑ፤ ሀገር እንሥራ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.