Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 57ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተፈረሙ ሶስት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡

የመጀመሪያው ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል የአራት መቶ ሰላሳ ሰባት ሚሊዮን አራት መቶ ሺ (437,400,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡

ሁለተኛው የማህበረሰብ ተኮር የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ (145,500,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡

ሶስተኛው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሀምሳ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ (54,600,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡

ምክር ቤቱም ሶስቱ የብድር ስምምነቶች ከሀገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ተቋማት ለሚሰጧቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቷል፡፡

ተቋማቱ ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች በውስጥ ገቢ የሚሸፈኑ ወጪዎችን ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች በሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ለመሸፈን እንዲችሉ የአገልግሎት ተጠቃሚውን አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት በጥራት መስጠት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንዲያስችሉ ረቂቅ ደንቦቹ ተዘጋጅተው ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. ከዚያም ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው ለኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ማቋቋሚያ ስምምነት የአባልነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክን በአባልነት መቀላቀሏ ለሀገራዊ የልማት ፋይናንስ፣ ለመሠረተ ልማት ድጋፍ እና ለማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት የሚያስችላትና ከደቡብ ደቡብ የፋይናንስ ሥርዓቶች ጋር የሚኖራትን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑ ስለታመነበት የባንኩን የመመስረቻ ስምምነት ለማጽደቅ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገራችን ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ በ2006 ዓ.ም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወጥቶ ላለፉት አመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡

በዚህም በኢንዱስትሪው አንዳንድ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም አለማችን ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ እድገት፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የመሰረተ ልማቶች ፍላጎት ማደግ አንጻር ሰፊ ክፍተት የነበረበት በመሆኑ የዘርፉን ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ፣ በስራ ላይ ያሉ የህግ ማዕቀፎችን በማጣጣምና በማዋሃድ እንዲሁም የዘርፉን የመልማት አቅም አሟጦ በመጠቀም የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ እንዲያስችል ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያያበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ከዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የከተማ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡

በ1997 ዓ.ም ወጥቶ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በስራ ላይ በቆየው የከተማ ልማት ፖሊሲ በከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ ከተሞች በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ እንዲሆን፣ የገጠርና ከተማ እንዲሁም የከተማ ከተማ ትስስር እንዲጠናከር፣ መሰረተ ልማትና የተለያዩ ማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲስፋፉ በተደረገው ጥረት ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ክፍተቶችም የነበሩበት ስለሆነ የነባሩን ፖሊሲ ክፍተቶች ለማረም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞች አካባቢ እየታዩ ያሉ አበረታች ለውጦችን ለማጽናት እና የበለጠ ለማጎልበት የከተማ ልማት ፖሊሲ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያያበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ከዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.