Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ ዐሻራ ትውልድን በፀና መሰረት ላይ ለማቆም ያስችላል – አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ላለፉት 7 ዓመታት ስትተገብር የቆየችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መጪውን ትውልድ በፀና መሰረት ላይ ለማቆም የሚያስችል ነው አሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን።

የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በዛሬው ዕለት ይፋ እየተደረገ ነው።

መርሐ ግብሩ በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ አኔዲማ ላይ በተጀመረበት ወቅት አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት 28 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል።

በዚህም በ8 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ መሸፈኑን ገልጸው፤ ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሆነ አንስተዋል።

ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃው የሀገር ሉዓላዊነትን በመስጠበቅ ሂደት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ዘንድሮ በክልሉ 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ከ1 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ዕቅድ መያዙን አንስተዋል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሸገር ከተማ ደረጃ እስካሁን 71 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ዘንድሮ 19 ነጥብ 1 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን አንስተው፤ የከተማዋን አረንጓዴያማነትን 27 በመቶ ለማድረስ ውጥን ተይዟል ነው ያሉት።

በታምራት ደለሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.