Fana: At a Speed of Life!

የባሕር በር ዲፕሎማሲ እና ለቀጣናዊ ትስስር…

የኢትዮጵያ የባሕር በር ዲፕሎማሲ በሳል አቀራረብና አርቆ አሳቢነት የታየበት ሲሆን፣ በቀጣናው ያሉ ውስብስብ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማስታረቅ ያለመ ነው፡፡

ይህ መርህ ለዘላቂ መፍትሔ ብቸኛው መንገድ ነው።

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ሕዝቧ እና በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው ኢኮኖሚዋ አስተማማኝ እና ቀጥተኛ የባሕር በር ማግኘትን የብሔራዊ ደኅንነት እና የህልውና ጉዳይ አድርጋዋለች።

የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ የባሕር በር ያጣችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በአንድ የወደብ አማራጭ ላይ ጥገኛ መሆኗ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የጂኦፖለቲካ ተጋላጭነት ዳርጓታል።

ይህንን ስትራቴጂካዊ ክፍተት ለመሙላት የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ሰላማዊ ውይይትን እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን መሠረት ያደረጉ መጠነ-ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት አይጋፋም፡፡ ይልቁንም የጋራ እድገትን የሚያረጋግጥ መሆኑን በተደጋጋሚ በዲፕሎማሲ መድረኮች ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ለዚህም ወደብ ለሚያቀርቡ የጎረቤት ሀገራት እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ወይም የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ ሀገራዊ ግዙፍ ተቋማትን በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

ይህ አካሄድ የጎረቤት ሀገራትን የኢኮኖሚ ጥቅም ከኢትዮጵያ ዕድገት ጋር በቀጥታ የሚያስተሳስር ስልት ነው።

ኢትዮጵያ በአንድ የጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ ያላትን የ95% የንግድ ጥገኝነት ለመቀነስ የዲፕሎማሲ አድማሷን አስፍታለች፡፡

ከኬንያ መንግሥት ጋር በመሆን የላሙ ወደብን፣ በባቡርና በመንገድ መሠረተ ልማት ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘት የቴክኒክና የፖለቲካ ስምምነቶች አድርጋለች፡፡

በተመሳሳይ የበርበራ ወደብን ለመጠቀምና አማራጭ የወደቦች ስትራቴጂን ለመጠቀም እየሰራች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ፍላጎቱን ለማሳካት ኃይልን ወይም ጦርነትን እንደማይጠቀም በተደጋጋሚ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አረጋግጧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን መሠረት፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስና የመጠቀም መብት እንዳላቸው የሚደነግገውን ዓለም አቀፋዊ መርህ መሠረት በማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ግፊቶችን እያደረገች ትገኛለች፡፡

በቀጣናው በተፈጠሩ የፖለቲካ ውጥረቶች ሳቢያ የባሕር በር ጥያቄው ወደ ግጭት እንዳያመራ ኢትዮጵያ በሦስተኛ ወገን ከዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጋር በቅርበት እየሰራች ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲና በሕጋዊ መንገድ የባሕር በር የምታገኝበትን መንገድ እያመቻቸች ነው፡፡

ጥረቱ በስኬት ሲቋጭ ኢትዮጵያ ለገቢ ወጪ ንግድ የምታወጣው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፡፡

ይህም ሉዓላዊነቷንም በማሳደግ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር ለቀጣናዊ ሰላም ትልቅ መሠረት ይጥላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.