ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ያቀረቡት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ ረቂቅ አዋጁ የካርበን ገበያ ስትራቴጂን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ነው ብለዋል፡፡
ይህም የፓሪሱን ስምምነት ጨምሮ ሀገራችን የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ውሎችና የገባቻቸውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ቃል ኪዳን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
ከፍተኛ ጥራት ላለው የአረንጓዴ ኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ ሸግግር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር አስፈላጊ የሆነውን የህግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አዋጁ ቀደም ሲል ያለበቂ የአሰራር ስርዓት ሲተገበር የነበረው የግብይት ሂደት በግልፅ የህግ ማዕቀፍ እንዲመራ ያስችላል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ አዋጅ ቁጥር 1436/2018 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።