Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከቡና ወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት ወደ ውጪ ከተላከ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጪ ንግድ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡
የኦሮሚያ ክልልም በዚህ ስኬት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በክልሉ የቡና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም የቡናን የዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሥራ ሲከናወን መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
በዚህ መሰረትም በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት ከ183 ሺህ 557 ቶን በላይ የቡና ምርት ከክልሉ ለውጪ ገበያ መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡
ለውጪ ገበያ ከቀረበው የቡና ምርትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ነው የተገለጸው፡፡
በቀጣይ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግና ጥራትን ለመጨመር በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በምርምር በመታገዝ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.