Fana: At a Speed of Life!

ም/ቤቱ ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ በርካታ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል – አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፉት 5 ዓመታት ለሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ በርካታ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ።

አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ባለፉት 5 ዓመታት የተከናወኑ የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከም/ቤቱ የአማካሪና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አፈ ጉባዔው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ምክር ቤቱ ባለፉት 5 ዓመታት ለሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ በርካታ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።

በተለይም ዘላቂ መግባባትን ለመፍጠር የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ያከናወናቸው ተግባራት ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ተስፋ የፈነጠቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከሕዝብ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን፣ የጸጥታና ደኅንነት ስጋቶችን አስመልክቶ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በአፈጻጸም ክፍተትና የኃላፊነት መጓደል በሚታይባቸው መሥሪያ ቤቶች ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ግልጽ አሠራር መዘርጋት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንደ ሀገር ትልቅ ስኬት የተመዘገበትና በርካታ መራጮች የተሳተፉበት እንዲሆን ምክር ቤቱ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን እና ለተመዘገቡት ውጤቶች የም/ቤቱ ጽ/ቤትና የሪፎርም ኮሚቴ ድርሻ የማይተካ እንደነበር አስረድተዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ÷ ምክር ቤቱ ተልዕኮዎቹን ለመወጣትና የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን አስገንዝበዋል።

በተለይም በክትትልና ቁጥጥር ሥራ ተጠያቂነትን ከኃላፊነት ጋር ለማረጋገጥ ስኬታማ ተግባራት እንደተከናወኑ መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.