Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ ዐሻራ ለአየር ንብረት ለውጥ እንደ መፍትሄ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለማችን ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን ላይ ከ1 ዲግሪ ሴልሺዬስ በላይ ጨምራለች።

ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን ደግሞ በፊት ከሚለቀቀው በእጥፍ ጨምሯል፡፡

እንደ ጥናቶች፤ ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ የሙቀት መጠኑ ወደ 4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ ሊልም ይችላል።

ይህ ማለት ዓለማችን አይታው የማታውቀውን ሙቀት በማስመዝገብ ህይወትን ማስቀጠል እጅግ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡

በሙቀት መጨመር ሳቢያ በሰዎች እንዲሁም ተፈጥሮ ላይ የሚከሰትን ጉዳት በተደጋጋሚ የምንሰማው ዜና ሆኗል፡፡

የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ የሰው ልጅ የተሰጠውን ተፈጥሮ ተንከባክቦና ጠብቆ ማቆየት ባለመቻሉ ነው፡፡

ከሰሞኑ በአውሮፓ የተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት የዚሁ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት በአውሮፓ ፈረንሳይ፣ ስፔንና ሌሎች ሀገራት የተከሰተው ከባድ ሙቀት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ነጥቋል፡፡

በፈረንሳይ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡

በከባድ ሙቀቱ ያስከተለው የሰደድ እሳት አደጋም ከፍተኛ መጠን ያለው ደን አውድሟል፤ ሰዎችንም ከቀያቸው አፈናቅሏል።

ይህ ክስተት የዓለም ሀገራት በተቀናጀ መልኩ ለመፍትሄ የማይተጉ ከሆነ አሁን የደረሰው ጉዳት በሚያስከፋ ደረጃ ከፍ እያለ መቀጠሉ አይቀርም፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ መቀነስ ግድ ይላል።

ይህንን ለማሳካት ደግሞ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርቦን የሚመጥ የደን ሀብት ያስፈልጋል።

በመሆኑም የተመናመነውን የደን ሽፋን በማሳደግ ወደነበረበት ለመመለስ ሀገራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። በአንድ ወቅት የደን ሽፋኗ ከ40 በመቶ በላይ የነበረው ኢትዮጵያ በአጠቃቀም ችግርና ከስር ከስሩ ባለመተካት የደን ሃብቱ ተመናምኖ ወደ 3 በመቶ ማሽቆልቆሉ ይታወሳል።

ከደን ሽፋን መቀነስ ጋር ተያይዞ የመጣው የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት ምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት መንጠፍ የሀገራችንን ህዝብ ለከፋ ድርቅና ከዛ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡

በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በመላ ሀገሪቱ የተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆና ተንከባክቦ በማቆየት፣ ተመናምኖ ወደ መጥፋት እያመራ የነበረውን የሀገሪቷን የደን ሽፋን በመመለስ ትልቅ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡

በመርሐ ግብሩ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ስራ ሽፋኑን 26 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ተግባር ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም የሆነ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሐ ግብር የሚካሄድባ ሀገር አድርጓታል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ካለው ትልቅ ሀገራዊ ተፈጥሮን የመጠበቅ ሚና ባሻገር በዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በመሳብ፤ አድናቆትና ምስጋናን የተቸረውና ሌሎች ሀገራት በአረዓያነት ወስደው የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል እየተገበሩት ነው።

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.