ከ18 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአማራ ክልል የመስህብ ሥፍራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ከ18 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ዜጎች በአማራ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል አለ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ።
የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ እንዳሉት ፥ በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በማልማት የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በዓመቱ ከ18 ሚሊየን በላይ ዜጎች በክልሉ የሚከወኑ ኃይማኖታዊና ባሕላዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችን እንደጎበኙ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም 58 ሺህ የውጭ ሀገራት ዜጎች በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ መስህቦችን ተመልክተዋል ብለዋል።
ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ጎብኚዎች 11 ቢሊየን ብር በላይ በክልሉ ማንቀሳቀስ መቻሉን አመልክተዋል።
የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የአገልግሎት ጥራት፣ የመስህብ ሀብት የመዳረሻ ልማት፣ የቅርስ እንክብካቤና ጥገና ሥራ ላይ በትኩረት መሰራቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ ከፍተኛ የቅርስ ክምችት መኖሩን አውስተው ፥ ቅርሶችን ለመንከባከብ 41 የመስህብ ሃብት ላይ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ከእነዚህ መካከል 9 ሙዚዬሞች እንደሚገኙበት እና ለዚህም የክልሉ መንግሥት ከ111 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መድቦ መስራቱን ጠቅሰዋል።
በዓመቱ ተዘርፈው ከሀገር የወጡ 19 ቅርሶችን ማስመለስ መቻሉንም ሃላፊው ተናግረዋል።
በ2019 በጀት ዓመት ከ100 ሺህ በላይ የውጭ ሀገርና 21 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ወደ ክልሉ በመሳብ ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ይሰራል ብለዋል።
በደሳለኝ ቢራራ