የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርት ሉዊስ የቀጥታ በረራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደሴቲቷ ሀገር ሞሪሺየስ ዋና ከተማ ፖርት ሉዊስ ከነገ ጠዋት ጀምሮ የቀጥታ በረራ ማድረግ ይጀምራል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤ የቀጥታ በረራው የሁለትዮሽ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ለሀገራቱ ዘላቂ እና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይዞ ይመጣል።
በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በባሕር ዳርጃዎቿ የምትታወቀው ሞሪሺየስ በታሪክና ባሕል ቱሪዝም ከበለፀገችው ኢትዮጵያ ጋር የቀጥታ በረራው መተሳሰር የቱሪስት ፍሰትን ያቀላጥፋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሞሪሺየስ አምባሳደር ኢንድራርጂት ባቡዋ በበኩላቸው፤ የቀጥታ በረራው በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሁለቱ ሀገራት ነጋዴዎች በቀላሉ እንዲገናኙ፣ የንግድ ልውውጥ እንዲያፋጥኑ እና የጋራ ኢንቨስትመንት እንዲያቋቁሙ ምቹ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
የሀገራቱን የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳደግ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና የባሕል ልውውጥን ለማጠናከር አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 145 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን በ41 የአፍሪካ ሀገራት 62 መዳረሻዎችን በማስፋፋት የአህጉሪቱን ብሎም ዓለም አቀፍ ትስስርን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
አየር መንገዱ ወደ ፖርት ሉዊስ ከተማ በሳምንት 3 ቀን በረራ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በታምራት ደለሊ