ሕዝባዊው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈ መርሐ ግብር ነው
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የበረሃማነት መስፋፋት እና የተፈጥሮ ሀብት መራቆት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ሥጋት በሆኑበት በዚህ ዘመን፣ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሕዝባዊ ንቅናቄ ሆኗል።
በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው ይህ ታላቅ ህዝባዊ እንቅስቃሴ፣ ከችግኝ ተከላ ዘመቻ አልፎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማቀፍ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ አስችሏል።
ይህ ስኬት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ትልቅ ትኩረትን ስቦ እውቅና እና ሽልማትን አስገኝቷል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለተከናወኑ የደን መልሶ ማልማትና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራዎች ከተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት አግኝታለች።
ኢትዮጵያ በጣሊያን ሮም ከተማ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በተከበረው 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል መድረክ ላይ በዘላቂ የደን አያያዝና አጠቃቀም ሽልማት ተቀብላለች።
ይህ ሽልማት ኢትዮጵያ በደን ሽፋን ፈጣን ዕድገት፣ በህዝባዊ የንቅናቄ ሞዴል፣ በምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ትሩፋት እንዲሁም በቀጣናዊ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ላስመዘገበቻቸው ስኬቶች የተሰጣ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ በተጀመረባቸው አጭር ዓመታት ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በማጽደቅ የሀገሪቱን አጠቃላይ የደን ሽፋን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ወደ ተሻለ ከፍተኛ ምዕራፍ ማድረስ ተችሏል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ያለ ምንም ልዩነት በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በመውጣት ያሳዩት ተሳትፎ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈጥሮ መራቆትን ለመከላከል ሊጠቀምበት የሚችል ታላቅ የሕዝብ አንድነትና ቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
አረንጓዴ አሻራ ከደን ዛፎች በተጨማሪ ሰፊ የፍራፍሬ (እንደ አቮካዶ፣ ማንጎና ፓፓያ) እና የእንሰሳት መኖ ዛፎች በመተከላቸው፣ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ኢትዮጵያ ከችግኞቿ ለጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በመስጠት የአረንጓዴ ዲፕሎማሲን አበርክታለች፡፡
ለኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተሰጠው ዓለም አቀፍ እውቅና ሀገሪቱ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እና ለዘላቂ ልማት ያላትን ጥልቅ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው።
ድሉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብርና የደከሙበት ጥረት ፍሬ ሲሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ ፅዱ፣ ለምለም እና የተሻለች ሀገርን ለማስተላለፍ የሚደረገውን ታሪካዊ ጉዞ ይበልጥ ያጠናክረዋል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በአረንጓዴ ልማት ያላትን ስም ከፍ ከማድረጉም በላይ፣ ሌሎች ሀገራትም ዱካውን በመከተል የአካባቢያቸውን ስነ-ምህዳር እንዲጠብቁ ትልቅ ተነሳሽነት ይፈጥራል።