Fana: At a Speed of Life!

ለዘመናዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምን እና አብሮነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሂደት ነው።
ሂደቱ የብዝሃነት ማዕቀፎችን በማክበር፣ የዜጎችን ተሳትፎ በማስፋት እና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ላይ የተመሰረተ ነው።
ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ውስጥ በርካታ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች።
ያለፉትን ታሪካዊ ስህተቶች ለማረም እና የተሻለች ሀገር ለመገንባት የንግግር እና የመመካከር ባህልን ማዳበር የግድ ይላል።
ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡
ምክክሩ ዜጎች በነፃነት የሚወያዩበትና የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ሂደቱ የመላዋን ኢትዮጵያ ስብጥር በማካተት ሁሉም ዜጋ በራሱ ቋንቋና ፍላጎት ሃሳቡን እንዲገልጽ አስችሏል።
እንደ ሀገር ለዘመናት የቆዩ የሀገረ መንግሥት ምስረታ፣ የሰላም ግንባታ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ይቻል ዘንድ የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ያለ እረፍት ሀገራቸውን እና የነገውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ እየመከሩ ነው።
አንዱ የሌላውን አተያይ በመረዳት ከኋላ ቀሩ የደም አፋሳሽ መንገድ በመውጣት በሰላማዊ ውይይት ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እየመከሩ ይገኛሉ።
በውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ የሚገኙ መፍትሔዎች ለነገዋ ሀገር ጠንካራ መሠረት የሚጥሉ፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ምዕራፍ የሚከፍቱና የጋራ አሸናፊነትን የሚያረጋግጡ ናቸው።
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፣ ኢትዮጵያውያን የጠብመንጃና የኃይል እሳቤን አስወግደው በሐሳብ የበላይነት የሚመሩበትን አዲስ ወርቃማ ዘመን ያበሰረ ክስተት ሆኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.